1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብሔራዊ ምክክር መድረኩ የማህበረሰቡን እኩል ተሳትፎ ያረጋገጠ መሆን አለበት መባሉ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 11 2016

``የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት እና የደህንነት ጥናት ኢንስቲቲዩት በጋራ በመተባበር ያዘጋጁት ይህ መድረክ ሃገራዊ ምክክሩ የተቀናጀ፣ አካታችነትን ያረጋገጠ እና ትርጉም ያለው እንዲሆን በሚደረገው ጥረት ላይ የራሱን አስተዋፅዎ ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል።``

https://p.dw.com/p/4ZGSt
Ethiopia / Addis Ababa National Dialogue
ምስል Hana Demise/DW

አካታች ሃገራዊ ምክክር እንዲኖር

ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የትርክት ልዩነት መፍትሄ ይሆናል ተብሎ የሚታሰበው ሀገራዊ ምክክር መድርክ  የማህበረሰቡን እኩል ተሳትፎ ያረጋገጠ እና  ትርጉም ያለው  መሆን እንዳለበት ተነገረ ። የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት እና የደህንነት ጥናት ኢንስቲቲዩት  በመተባበር ባዘጋጁት የውይይት መድረክ፣ በማህበረስቡ ዘንድ  የሚገለሉ እና አናሳ የሚባሉት የማህበረሰብ ክፍል  የሚደርስባቸው በደል እና ጫና እንዴት ማቆም እና በዚህ  የሀገራዊ ንግግር ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ መሰራት  ይኖርበታል ተብሏል ። 

በኢትዮጵያ ሊደረግ ለታሰበው ሀገራዊ ምክክር  መድረክ የተቀናጀ፣ አካታች እና ውጤታማ  እንዲሆን  እየተሰራ ያለውን ጥረት ለማገዝ በተዘጋጀው  ኮንፈረንስ  ንግግራቸውን ያደረጉት ዶ/ር አሉላ ፓንክረስት፤  አናሳ የሚባሉት የማህበረሰብ ክፍሎች በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ እንዲካተቱ ግልጽ  እንቅስቃሴ እና ጥረት ያስፈልጋል ብለዋል። በሽመና እና በ ሽክላ ስራ የሚተዳደሩ ማህበረሰቦች የሚገለሉ እና በቁጥር አናሳ ቢሆኑም  በተለያየ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚኖሩ በመሆናቸው የሀገራዊ  ምክክር መድረኩ እነኝህን የማህበረሰብ ክፍል ማካተት  ይገባል ሲሉ ለ DW ተናግረዋል።

ዶክተር አሉላ ከ 5 አመት በፊት ተደርጓል ባሉት ጥናት በሀገሪቱ ውስጥ አሁንም ድረስ መገለል  ይደርስባቸዋል  ባሉት የማህበረሰብ ክፍል በየአካባቢው በኢኮኖሚው እና በአገልግሎት  ከፍተኛ ድርሻ ቢኖራቸውም እስካሁን  ተንቀው እና ተገለው እንደሚኖሩ አስረድተዋል።  

ይካሄዳል የተባለው የምክክር  መድረክ የራሱ የሆነ መንደር መፍጠር  በመሆኑ  ሴቶች መካተት ይኖርበታልተብሏል።  ምንም እንኳን  በሀገሪቱ ካለው የህዝብ ብዛት 58.9 ሴቶች  ቢሆኑም  ከ 30% በታች  መወከላቸው በቂ ባይሆንም  ብልጥ ልጅ የያዘውን ይዞ ያለቅሳል ነው እና እረፍዶብኛል ብለን መስራት አለብን ሲሉ   ለDW የተናገሩት  ፅሁፍ አቅራቢ መሰረት ተጫኔ ከአዲስ አበባ ዩኒቪርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ናቸው።  

በኢትዮጵያ ሴቶች ከአርበኝነት እስከ ሀገር መሪነት የበቁበት ታሪክ ነው ያለን ያሉት መሰረት ጫኔ ሴቶችን በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ብቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ  አስገዳጅ ሁኔታዎች እንዲፈጠር ማድረግ በተጨማሪም ሴቶች በአንድም በሌላም ይሁን አውቀው እና ሳያውቁት እራሳቸውን በማይጠቅም ጉዳይ ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ ይህንን በማስተዋል ማቆም እና በጋራ መቆም ይኖርብን ብለዋል።  

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት እና የደህንነት ጥናት ኢንስቲቲዩት  በጋራ  በመተባበር ያዘጋጁት ይህ መድረክ ሃገራዊ ምክክሩ የተቀናጀ፣ አካታችነትን ያረጋገጠ እና ትርጉም ያለው እንዲሆን በሚደረገው ጥረት ላይ የራሱን አስተዋፅዎ ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል ።

ሃና ደምሴ

አዜብ ታደሰ

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር