1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን ተቀባይነት ያላገኙ ተገን ጠያቂዎችን በፍጥነት ለማስወጣት ሕግ አፀደቀች

ማክሰኞ፣ ጥር 14 2016

የጀርመን ፓርላማ ያልተሳካላቸው ጥገኝነት ጠያቂዎችን በቀላሉ እና በፍጥነት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ያለመ ረቂቅ ህግ ያለፈው አርብ አጽድቋል። አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የረድዔት ድርጅቶች ግን ድንጋጌዎቹን ተቃውመው ተችተዋል።

https://p.dw.com/p/4bU9g
የጀርመን ፓርላማ ያልተሳካላቸው ጥገኝነት ጠያቂዎችን በቀላሉ እና በፍጥነት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ያለመ ረቂቅ ህግ በዚህ ሳምንት አጽድቋል
የጀርመን ፓርላማ ያልተሳካላቸው ጥገኝነት ጠያቂዎችን በቀላሉ እና በፍጥነት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ያለመ ረቂቅ ህግ በዚህ ሳምንት አጽድቋልምስል Kay Nietfeld/dpa/picture alliance

የጀርመን ምክር ቤት ተቀባይነት ያላገኙ ተገን ጠያቂዎችን የሚመለከት ህግ አፀደቀ

ቡንደስታግ እየተባለ የሚጠራው የጀርመን ፓርላማ ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያላገኙ ተገን ጠያቂዎችን በፍጥነት ከጀርመን ማስወጣትን የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅን ያለፈው ሳምንት መጨረሻ በጎርጎሪያኑ ጥር 19 ቀን 2024 ዓ/ም አጽድቋል። ርምጃው የተወሰደው የመራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ጥምር መንግስት መደበኛ ያልሆነ ስደትን እና ተያያዥ ጉዳዮችን ለመፍታት ማቀዱን ተከትሎ ነው።
ህጉ ከገና በፊት በነበረው አንድ ሳምንት  በአጭር ጊዜ የተነሳ አጀንዳ ሲሆን፤ ምክንያቱ ደግሞ ከጥምር አጋሮቹ አንዱ የሆነው አረንጓዴው ፓርቲ ለውጥ እንዲደረግ በመጠየቁ ነው።
የሶስቱ የጥምር መንግስቱ  መስራቾች ገዥ ፓርቲዎች ህጉን ደግፈው ድምጽ ሰጥተዋል።  በጣት የሚቆጠሩ የአረንጓዴው ፓርቲ አባላት እና የተቃዋሚው የክርስቲያን ዴሞክራቶች ፓርቲ እና አማራጭ ለጀርመን የተባሉ ፓርቲዎችም ውጤታማ የማይሆን ሲሉ ርምጃውን ተቃውመው መንግስትን ተችተዋል።ህጉ ያለፈው ሀሙስ ክርክር የተደረገበት ሲሆን በማግስቱ አርብ በጀርመን ፓርላማ እንዲፀድቅ መደረጉን በጀርመን ሀገር የህግ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።የተገን ጠያቂዎች ጥረዛ በጀርመን  

የጀርመን ፓርላማ ያልተሳካላቸው ጥገኝነት ጠያቂዎችን በቀላሉ እና በፍጥነት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ያለመ ረቂቅ ህግ አጽድቋል
የጀርመን ፓርላማ ያልተሳካላቸው ጥገኝነት ጠያቂዎችን በቀላሉ እና በፍጥነት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ያለመ ረቂቅ ህግ አጽድቋልምስል C. Ohde/blickwinkel/McPHOTO/picture alliance

ከሕጉ አንዳንድ ድንጋጌዎች  መካከል ወደ አገር ቤት የመመለሻ ማሻሻያ ህግ ተብሎ የሚጠራው ሲሆን፤ ይህም ከስደት በፊት ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ጥበቃ ሲሆን ይህም  አንድ ግለሰብ ጀርመንንን ከመልቀቁ በፊት ሂደቱን ማጠናቀቅ እንዲችል ለባለሥልጣናት ተጨማሪ ጊዜ የሚሰጥ ነው።
 ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ እንደሚሉት ጥገኝነት ጠያቂዎቹ ከሀገር ከመባረራቸው በፊት ከዚህ በፊት የነበረው ከፍተኛው የእስር ጊዜ 10 ቀን ሲሆን በአዲሱ ህግ ግን ወደ 28 ቀናት ይራዘማል።

በድንጋጌው መሠረት ተገን ጠያቂዎች  ከየፌዴራል ግዛቶቹ «በፍጥነት» ሊወጡ ይችላሉ ብለዋል የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፌዘር
በድንጋጌው መሠረት ተገን ጠያቂዎች ከየፌዴራል ግዛቶቹ «በፍጥነት» ሊወጡ ይችላሉ ብለዋል የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፌዘርምስል Sebastian Willnow/dpa/picture alliance

ይህ ድንጋጌ ባለስልጣናት ፍተሻዎችን በሚያደርጉበት ጊዜ ተጨማሪ ስልጣን ይሰጣል።ይህም  ከዚህ በፊት  ባለስልጣናት ወደ ሀገር ቤት የሚላከው ግለሰብ ክፍል ብቻ ለፍተሻ እንዲገቡ ይፈቀድ የነበረ ሲሆን፤ በአዲሱ ህግ  የጋራ  ክፍሎችን ጭምር  ገብተው እንዲፈትሹ ይፈቀድላቸዋል።
ይህም ተባባሪዎችን ጭምር በማግኘት ተገን ጠያቂዎችን በቀላሉ ከጀርመን ለማስወጣት እና አንዳንድ ጊዜም ወደ ሀገራቸው ላለመመለስ የመታወቂያ ወረቀቶችን መስጠት በማይፈልጉ ስደተኞች ሂደቱ እንዳይዘገይ  ወይም እንዳይደናቀፍ የባለስልጣናትን ስራ ያቀላል ተብሏል። ከዚህ በተጨማሪ የተደራጁ ወንጀሎችን የሚፈፅሙ እና በህገወጥ የሰዎች ዝውውር የሚሳተፉ ሰዎችን ለመያዝም ህጉ ለባለሥልጣናት ያግዛል።
የህግ ባለሙያው እንደሚሉት ከኢትዮጵያውያን ስደተኞች አንፃር ህጉ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተለዬ ነገር የለውም።

የጀርመን የስደተኞች ጉዳይ ረቂቅ ህግ
ህጉን፤ እንደ ጀርመን የህግ ባለሙያዎች ማህበር ያሉ የመብት ተሟጋቾች ነቅፈውታል። ማህበሩ አያይዞም የሰላማዊ ሰዎችን ጥበቃ እና ደህንነት ላለማደናቀፍ  በጥምረት ስምምነቱ የገቡትን ቃል አጥፈዋል።ሲል ወቅሷል።

በባህር ላይ የስደተኞችን ህይወት የሚታደገው ሲ ረስኪዩ  የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በበኩሉ ህጉን «አስፈሪ»ሲል ገልጾታል። ህጉ ስደተኞችን እና የሰብአዊ እርዳታ የሚሰጧቸውን ሰዎች ጭምር ለእስር ቅጣት የሚዳርግ በመሆኑ ማዘናቸውን  የረዴት ድርጅቱ ሰብዓዊ  እርዳታ ቡድን ተናግሯል።

በባህር ላይ የስደተኞችን ህይወት የሚታደገው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በበኩሉ ህጉን «አስፈሪ»ሲል ገልጾታል
በባህር ላይ የስደተኞችን ህይወት የሚታደገው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በበኩሉ ህጉን «አስፈሪ»ሲል ገልጾታልምስል Raphael Schumacher/ SOS Humanity

በአንዳንድ ሁኔታዎች አዲሱ ህግ በጎ ፈቃደኞችን ጭምር ለእስር ሊዳርግ  የሚችል ነው።ብሏል ድርጅቱ።ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ግን የድርጅቶቹ ወቀሳው ህጉን ስራ ላይ ከመዋል አያግደውም ብለዋል።

ሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፌዘር  «የመቆየት መብት የሌላቸው ሰዎች አገራችንን በፍጥነት ለቀው እንዲወጡ እናደርጋለን» ሲሉ።ያለፈው ሐሙስ አመሻሽ ላይ በጀርመን ፓርላማ በተደረገው  ክርክር ህጉን ደግፈዋል።

የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፌዘር  «የመቆየት መብት የሌላቸው ሰዎች አገራችንን በፍጥነት ለቀው እንዲወጡ እናደርጋለን» ሲሉ። በጀርመን ፓርላማ በተደረገው ክርክር ህጉን ደግፈዋል
የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፌዘር «የመቆየት መብት የሌላቸው ሰዎች አገራችንን በፍጥነት ለቀው እንዲወጡ እናደርጋለን» ሲሉ። በጀርመን ፓርላማ በተደረገው ክርክር ህጉን ደግፈዋልምስል MICHELE TANTUSSI/AFP

የተገን ጠያቂዎች ጥረዛ በጀርመን  

ቀደም ሲል በተወሰዱ እርምጃዎች  ወደ ሀገራቸው የሚመለሱ ሰዎች ቁጥር በ2023  ዓ/ም በ27 በመቶ ማለትም ወደ 16,430 ከፍ ማለቱን ፌዘር አመልክተዋል።ከዓዲሱ ህግ በኋላም ከጀርመንን የሚባረሩ  ምክንያታቸው ተቀባይነት ያላገኙ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተገልጿል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


ፀሀይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ